የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትን እና ዲጂታላይዜሽንን ለማስፋፋት ዳይናሚክ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም (አ.ማ) እና በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል ክፍያ ሰነድ አውጪ የሆነው ካቻ ዲጂታል ፋይናንሺያል ሰርቪስ (አ.ማ) መካከል ወሳኝ የስትራቴጂክ ስምምነት ተፈርሟል።
ይህ ስምምነት አስፈላጊ መስፈርቶችን አሟልቶ በብሔራዊ ባንክ የጸደቀ ሲሆን፣ የመጀመሪያ መርሀ ግብሩ በዳይናሚክ ማይክሮፋይናንስ ዋና መሥሪያ ቤት ተካሂዷል።
ይህ ስትራቴጂክ ስምምነት የኢትዮጵያን የፋይናንስ አገልግሎት ዘርፍ በፈጠራ፣ በቴክኖሎጂ እና በውህደት ለማዘመን የተደረገ የጋራ ቁርጠኝነት መሆኑን ያሳያል ተብሏል።
በዚህ ስምምነት መሠረት፣ የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎቶች በዲጂታል መልክ እንዲቀርቡ እና በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ታቅዷል። ይህም ደንበኞች ወደ ቅርንጫፍ መሄድ ሳይጠበቅባቸው በሞባይል ስልካቸው ብቻ ምቹ የፋይናንስ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ያስችላል።
ተቋማቱ በጋራ ኮ-ብራንድ የሞባይል መተግበሪያ እና USSD አገልግሎት ጀምረዋል። እነዚህ መፍትሄዎች የተለያዩ የዲጂታል ቁጠባ አገልግሎቶች፣ ቁጠባ-ላይ የተመሰረተ ብድር፣ የደመወዝ መዳረሻ ብድር፣ ለአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ አገልግሎቶች፣ የእርሻ ብድር እና የ«አሁን ይግዙ፣ በኋላ ይክፈሉ» አማራጮችን ያካትታሉ።
እነዚህ አገልግሎቶች ለተለያዩ የገቢ ደረጃዎች እና የኢኮኖሚ ዘርፎች የሚገኙ ደንበኞች የዕለት ተዕለት የፋይናንስ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት ታስበው የተዘጋጁ መሆናቸው ተገልጿል።